| « Eight Ethiopian Maids found dead in United Arab Emirates | Ethiocross's Song of the week by Dr. Dereje Kebede " yamliko netsanet" » |
ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ቅዱስ ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ ተወያዩ
ሪፖርተር [በታምሩ ጽጌ]
ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 3 ቀን 2001 ዓ.ም. ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ቅዱስ ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳቱ ከተወያዩ በኋላ በቤተ ክርስቲያን ሕግ መሠረት ችግራቸውን እንዲፈቱ አሳሰበ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ በነገው ዕለት ስብሰባውን እንደሚጀምር የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ገለጸ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ አባይ ፀሐዬ፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተ/ማርያም፣ የፌዴራል ፖሊስ ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በተገኙበት፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት በተደረገ ውይይት፤ መንግሥት ጣልቃ ከመግባቱ በፊት ጳጳሳቱ ተወያይተው ችግራቸውን በመፍታት ሃይማኖታቸውን መምራት እንደሚገባቸው የመንግሥት ተወካዮቹ አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይ ከሌሎቹ አኅጉረ ስብከቶች አድባራትና ገዳማት ጉዳይ የተለየ መሆኑን የገለፁት አቶ አባይ ፀሐዬ፣ ነገሮቹን በትዕግሥትና በእርጋታ ተነጋግረው በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት መፍታት ካልቻሉ መንግሥት ዝም ብሎ እንደማያይ ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ከተለያዩ አካላት የሚፃፍላቸው ደብዳቤ ቢሮአቸውን እንዳጨናነቀው መናገራቸውን የገለፀው ጽ/ቤቱ፣ በእርጋታ ተነጋግረው ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት እንዲሰፍን ማድረግ እንዳለባቸው ማሳሰባቸውን ጽ/ቤቱ ገል..ል፡፡
በስብሰባው ላይ 37 ሊቃነ ጳጳሳት እንደተገኙ የገለፀው ጽ/ቤቱ፣ ሲኖዶሱ ያቋቋመው ኮሚቴ ለምን ተበተነ? የሀገረ ስብከቱ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እግድ ይነሳና ሌሎችንም ነጥቦች የተነሱ መሆናቸውንና የመንግሥት ተወካዮችም ”ይኸንን ሰኞ ተሰብስባችሁ ተመካክራችሁና ተነጋግራችሁ የምትፈቱት ነው” በማለት ምላሽ እንደሰጡ ተናግሯል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ ስብሰባውን እንደሚመሩ ለመንግሥት ተወካዮቹ ቃል መግባታቸውን የገለፀው ጽ/ቤቱ፣ ብፁዕ አቡነ ሣሙኤል የተወሰደባቸው መኪና እንደተመለሰላቸው፣ የእግዱ መነሳትና ወደ ቢሮአቸው የመመለሱ ጉዳይ ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው ስብሰባ እንደሚታይ ተናግሯል፡፡
ባለፉት ሦስት ሣምንታት በቤተ ክህነት ዙሪያ ለተፈጠረው ውዝግብ ከሰኔ 29 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶሱ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሂዳል ተብሎ ሲጠበቅ ስብሰባው ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ከሦስት ቀናት በኋላ ሐምሌ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. በድጋሚ እንደሚሰበሰብ ቢገለፅም ስብሰባው አልተደረገም፡፡ በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ቅዱስ ፓትርያርኩን ጠይቀን፤ የቤተ ክርስቲያኗ ፍትሕ መንፈሳዊ መምሪያ ተወካይ እንዲያነጋግሩን አድርገዋል፡፡
የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ስለታገዱበት ምክንያትና በሌሎች አፋጣኝ ውሳኔ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ አቅርቧቸው በነበሩት መነጋገሪያ አጀንዳዎች ስምምነት ላይ ባለመደረሱ ስብሰባው አለመካሄዱን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ተከታታይና አስፈፃሚ ተወካይ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ገልፀዋል፡፡
ሐምሌ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. የሲኖዶሱ አባላት ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ በመሄድ እንዲሰበስቧቸው ሲጠይቁ፤ “የመጣችሁት ወይም የተጠራችሁት ስብሰባ ለማካሄድ ሳይሆን ሐምሌ 5 ቀን 2001 ዓ.ም. የቤተ ክርስቲያኒቱ በዓለ ሲመትና ኢትዮጵያ የራሷን ፓትርያርክ የሾመችበትን 50ኛ ዓመት ለማክበር በመሆኑ ለሌላ ጉዳይ አልሰበስባችሁም” ማለታቸውን ተወካዩ ገልፀዋል፡፡
ከተሰበሰቡት የሲኖዶሱ አባላት መካከል የተወከሉት አምስት ጳጳሳት [አቡነ ማቴዎስ፣ አቡነ ማርቆስ፣ አቡነ ሉቃስ፣ አቡነ እንባቆም እና አቡነ ሳዊሮስ] ተፈራርመው በድጋሚ በደብዳቤ እንዲሰበስቧቸው ይጠይቃሉ፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ የሊቃነ ጳጳሳቱ ተወካዮች በደብዳቤ እንዲሰበስቧቸው የጠየቋቸውን በመቀበል “አጀንዳችሁ ምንድነው? ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅም ከሆነ እሰበስባችኋለሁ፡፡ የማይጠቅም ከሆነ አልሰበስባችሁም” በማለት አጀንዳዎቻቸው እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን ሊቀ ካህናት ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
የሲኖዶሱ አባላት አጀንዳ ለማቅረብ በተስማሙት መሠረት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚታየውን የአስተዳደር ችግር በጥልቀትና በስፋት እንዲከታተልና መፍትሄ የሚሰጥ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶሱ የሆነው ኮሚቴ ለምን ተሻረ?፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ለምን ታገዱ?፣ በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ላይ ስለወጣው መጽሐፍ ጉዳይ፣ የክርስቲያናዊ ልማት ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዴት ተሾሙ፣ ሰኔ 18 ቀን 2001 በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተሰብስበው ስለነበሩት፣ ሰራተኞችና የአድባራትና ገዳማት አለቆች ስብሰባ በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶሱ ያልተሰበሰበበትን ምክንያት እና በኢንተርኔት ማስቀደስ ስለተባለው ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጥበት አጀንዳቸውን ማቅረባቸውን ተወካዩ ገልፀዋል፡፡
ፓትርያርኩ ሊቃነ ጳጳሳቱ ያቀረቡትን አጀንዳ ከተመለከቱ በኋላ፣ በተነሱት ነጥቦች ላይ ከመነጋገራቸው በፊት ያዘጋጁትን ሪፖርት እንዲያዳምጡአቸው ሲጠይቁ ሰባቱ ጳጳሳት [አቡነ ቄርሎስ፣ አቡነ ፋኑኤል፣ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ አቡነ ሣሙኤል፣ አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ ሉቃስና አቡነ ዲዮስቆሮስ] “ሪፖርት ማዳመጥ አንፈልግም፡፡ ባቀረብናቸው ነጥቦች ላይ ብቻ ነው መነጋገር የምንፈልገው” በማለት ረግጠው መውጣታቸውን ተወካዩ ተናግረዋል፡፡
የሲኖዶሱ አባላት 51 ቢሆኑም ሐምሌ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተገኙት 37 ሊቃነ ጳጳሳት ሲሆኑ ሰባቱ ስብሰባውን ረግጠው በመውጣታቸው ያዘኑት ፓትርያርኩ፣ “በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሕግና ስርዓት የምንወያይ ከሆነ በሩ ክፍት ነው፤ ካለበለዚያ ግን እኔ የተሸራረፈ ስርዓትና ሕግ ለሚቀጥለው ትውልድ አላስተላልፍም፡፡ ይኸም የተሞከረውም ትልቅ ስህተት ነው፤ በዚህ ልንቀጥልበት አንችልም” በማለት ለቀሪዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ተወካዩ አስረድተዋል፡፡
ቀጣይ ሁኔታው ምንድነው የሚሆነው? መንግሥትስ ጣልቃ የገባበት ወይም የሚገባበት ሁኔታ ይኖራል? በሚል ለተጠየቁትም ሲመልሱ፣ መንግሥት እስካሁን ባለው ሁኔታ ጣልቃ አልገባም፡፡ አሁን ግን ስርዓተ አልበኝነት እየነገሰ መሆኑንና ፓትርያርኩ አያዙንም የሚል ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ችግር ነው፡፡ ሕዝብና ሕዝብን አጋጭቶ ደም እስኪፋሰስ መንግሥት ዝም ብሎ የሚያይ አይመስለንም፡፡ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር በፈቀደው መልኩ እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
“አንተም ተው፤ አንተም ተው” የሚል ሽማግሌ በመጥፋቱ፣ ሁሉም በፈቀደውና በፈለገው መንገድ መጓዝ መጀመሩን የገለፁት ተወካዩ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ምዕመናን ተሰባስበው ቀደም ብሎ እንደሚደረገው ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በመሆን ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል፡፡
ሐምሌ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. ሊደረግ በነበረው ስብሰባ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሊያቀርቡት ነበር በተባለው መግለጫ ላይ ተገለጹ ከተባሉት ጉዳዮች መካከል የቤተ ክርስቲያኒቱን ውሳኔዎች መፈፀሙንና አለመፈፀሙን እንዲከታተል የተሰየመው ኮሚቴ ለስውርና ድብቅ ዓላማዎች እንዲውል ለማድረግ ረዳት ሊቀ ጳጳሱ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር፤ ማለትም፣ ሠራተኞችን እንደሚያስተዳድር፣ እንደሚቆጣጠርና ውሳኔ እንደሚሰጥ፣ ቃለ አዋዲውን በመፃረር ስልጣን የመቀማትና ሌላ የመቅጠር፣ ዕድገት መስጠት፣ ማዛወር የማገድና የማስፈራራት ሥራዎችን ይሰሩ እንደነበር ሰነዱ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ ማንኛውም ሰው በኢንተርኔት ማስቀደስ እንደሚችል የሚሉና ሌሎችም የረዳት ጳጳሱን ስህተቶች የሚያሳዩ 20 ነጥቦችን ዘርዝረው እንደነበር ተወካይ ገልፀዋል፡፡
“ሃይማኖት አያጣላም፤ ፍላጐት ግን ያጣላል” ያሉት ሊቀ ካህናት ጌታቸው፣ ቅዱስ ፓትርያርኩን “አርጅተዋል በቡራኬ ይቆዩ” በማለት “እንደራሴ መሆን፣ ፓትርያርክ መሆን” የሚፈልጉ ክፍሎች መኖራቸውን ገልፀው “እግዚአብሔር ካልሾመው ሰው ምንም ዓይነት ስልጣን አያገኝም” ብለዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያኗ ርእስ በመሆናቸው፣ ብፁዕ አቡነ ሣሙኤልን ከኃላፊነታቸው አገዱ እንጂ ሥልጣነ ክህነታቸው አለመነካቱንና እግዳቸውም እልባት የሚያገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ መሆኑን ተወካዩ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር 200 የሚደርሱ አድባራትና ገዳማት እንደሚገኙ የገለፁት ሊቀ ካህናት ጌታቸው፣ ሁሉም አስተዳዳሪዎች [ከአምስቱ በስተቀር] ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተሰባስበው የአስተዳደር በደሎች፣ የሙስና መስፋፋት፣ ሠራተኞች ከሥራቸው ተባረው በስደት መኖር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ እየተስፋፋ የመጣው በረዳት ጳጳሱ ምክንያት መሆኑን በመግለፅና የአቋም መግለጫ በማውጣት እንዲታገዱላቸው በጠየቁት መሠረት እንጂ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከሳቸው ጋር የተለየ ፀብ ኖሯቸው አለመሆኑን አስምረውበታል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሣሙኤል፣ “እኔን ሊያነሳኝም ይሁን ሊሾመኝ የሚችለው ቅዱስ ሲኖዶሱ እንጂ ቅዱስ ፓትርያርኩ አይደሉም” በማለት በሌለ ውክልና የተፃፈባቸው እግድ በአስቸኳይ እንዲነሳ መጠየቃቸውን “ትልቅ ስህተት” የሚሉት ተወካዩ፤ “ማንም ምዕመን ሊገነዘበውና ሊያውቀው የሚገባው ነገር ቢኖር፣ ቅዱስነታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ ጠባቂ፣ አስተዳዳሪና የሲኖዶሱ ሰብሳቢ መሆናቸውን ነው” ብለዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ ስትመራ የቆየችው በቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ በፍትሕ መንፈሳዊና በዲድስቅልያ ሕግጋት መሆኑን የገለፁት ሊቀ ካህናት ጌታቸው፤ ቅዱስ ፓትርያርኩም ስልጠናቸውን ያገኙት በእነዚሁ ሕጐች አማካይነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ የጣሊያን መንግሥት ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ ወደ ሮም ለቤተ ክርስቲያን ሥራ ሰኔ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. መሄዳቸውን ተከትሎ፣ “የቤተ ክርስቲያናቱ አገልጋዮች በችግር ላይ እያሉ፣ ፓትርያርኩ በቤተ ክህነቱ ወጪ ይንሸራሸራሉ” በማለት በየአድባራቱና ገዳማቱ ላሉ ኃላፊዎች ደብዳቤ በመበተን ወደ አልተፈለገ ሥራ ውስጥ የገቡት ረዳት ሊቀ ጳጳሱና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ቢሆኑም፣ የኮሌጁ የበላይ ጠባቂ በደብዳቤና በአካል በመገኘት ይቅርታ በመጠየቃቸው ይቅርታ እንደተደረገላቸው ተወካዩ ተናግረዋል፡፡
አቡነ ሣሙኤልን ትላንት በተንቀሳቃሽ ስልካቸው አግኝተን ለማነጋገር ሞክረን ስልኩን ሌላ ግለሰብ በማንሳት “የእሳቸው ሐሳብ በሌሎች ጋዜጦች የተነገረ ስለሆነ የምንጨምረው የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሆኖም የአሜሪካ ድምፅ [ቪኦኤ] ዓርብ ምሽት የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቡነ ጢሞቴዎስን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በተደረገው ውይይት “እያንዳንዱ የሲኖዶስ አባል አሳምሞትና ያዝንበት የነበረው ሕገ ቤተ ክርስቲያንና ቃለ አዋዲውን 17 ዓመት ሙሉ አልተጠቀምንበትም ሲል ይገልጽ ነበር” ብለዋል፡፡
“ሲኖዶስ የወሰነውን ኮሚቴውን ማፍረስና ሊቀ ጳጳስ ማገድ የመሳሰለው ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ነው” የሚል መነሻ እንዳላቸው የገለጹት አቡነ ጢሞቴዎስ፣ “ሐምሌ 5 ቀን በዓለ ሲመታቸውን የቤተ ክርስቲያን በዓላችን ስለሆነ እናከብራለን፤ ከሰኞ ጀምሮ ሲኖዶሱ ስብሰባውን ያደርጋል፤ መስመርም እናስይዘዋለን” ብለዋል፡፡
የሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ አቡነ ማቴዎስ፣ የታገዱት አቡነ ሣሙኤል ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በተደረገው ውይይት ላይ መገኘታቸውን “ቤታቸው ተከቧል” የተባለው መንግሥት ለሳቸው ጥበቃ ለማድረግ ሲል የወሰደው እርምጃ መሆኑን መረዳታቸውን ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡ ከሹፌራቸው የተወሰደው የመኪና ቁልፍም እንደተመለሰላቸውና የታሸገው የሀገረ ስብከቱ ቢሮ ከነገው ስብሰባ በኋላ ሊከፈት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
Source:- ሪፖርተር
Related Story:- ስብሰባው ያለምንም ውሳኔ ተበተነ
ደጀ ሰላም :ዛሬ ጠዋት የጀመረውና አቡነ ጳውሎስን “ሲለምንና ሲማጸን” የዋለው የቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ያልምንም ውሳኔ፣ የፓትርያርኩ ዉሳኔም ሳይቀለበስ መበተኑን የደጀ ሰላም ሪፖርተሮች ከሥፍራው አስታውቀዋል።
ገና ከጠዋቱ ሕገ ቤተ ክርስቲያንና የስብሰባ ደንብ ያልነበረው ጉባዔው “እርስዎ መሰብሰብ አይችሉም” ማለት ሲገባው ያንን ሳያደርግ በመቅረቱ ሲታመስ ውሎ ንፋስ እንደገባው አቧራ ተበትኖ አድሯል። ከ45 ያላነሱ ቅ/ሲኖዶስ አባላት የተገኙበት ይህ ጉባዔ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ የቅዱስ ሲኖዶስን ሥልጣን በይፋ ለፓትርያርኩ በማስረከብ “ቅዱስ ሲኖዶስን ያፈረሰ ጉባዔ ተብሎ ሊጠቀስ ይገባዋል” የሚሉ አሉ።
በነገሩ የተበሳጩት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ስብሰባውን ጥለው ሲወጡ እነ አቡነ ገብርኤል ደግሞ ለቅዱስነታቸው የሥልጣን ዘመን መርዘም ሲከራከሩ ተሰምተዋል። ባለፈው ሳምንት የስብሰባ ሒደት የፓትርያርኩ”ደጋፊ” ተብለው የተፈረጁት ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ከሌሎቹ በተሻለ ሕግንና የስብሰባ ሥርዓትን ለማስጠበቅ ሲሞክሩ ውለዋል ተብሏል።
ነገሩ በዚሁ ስላለቀ፣ ነገ ማክሰኞም የአጋዕዝተ ዓለም ሥላሴ በዓለ ንግስ በመሆኑ ስብሰባው ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም።
ደጀ ሰላም በበኩሏ “ምንም የማይሳነው፣ ታሪክን መለወጥ የሚችለውን አምላክ ተስፋ እናድርግ፣ ቸር ወሬ ያሰማን” ትላለች ።
ደጀ ሰላም በበኩሏ “ኢታርዕየነ ሙስናሃ ለቤተ ክርስቲያን - የቤተ ክርስቲያንን ጥፋት አታሳየን፤ ምንም የማይሳነው፣ ታሪክን መለወጥ የሚችለውን አምላክ ተስፋ እናድርግ፣ ቸር ወሬ ያሰማን” ትላለች ።
Source:- ደጀ ሰላም
Trackback address for this post
Trackback URL (right click and copy shortcut/link location)
Feedback awaiting moderation
This post has 2 feedbacks awaiting moderation...